የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም አፊ አዟልና መንፈሱም ሰብስቧቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም። ኢሳ ፴፬፡ ፲፮።

 

ቅዱሳት መጻሕፍት የነፍስ ምግቦች ናቸው። እኛ ሰዎች ለቁመተ ስጋ ምግብና ውኃ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ነፍሳችን ደግሞ እንዲሁ ምግበ ነፍስ ያስፈልጋታል። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ምድራዊ ሕይወታችንን ጭምር እንዴትና በምን አኳኋን ማራመድ እንደሚገባን የሚያስተምር የሚመክርና የሚገስፅ መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው ታላቅ የሕይወት መመሪያ መሆኑን እንገነዘባለን። ስለሆነም የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርት ለተግሣፅ ልብንም ለማቅናት በፅድቅም ለሰው ምክር የሚጠቅም ነው። ፪ኛ ጢሞ ፫፡ ፲፮።

መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ምን ማለት ነው

መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ሐረግ “መጽሐፍ” እና “ቅዱስ” ከሚለው ሁለት ቃላት የተገኘ ሐረግ ሲሆን መጽሐፍ የሚለው ቃል ተጠቃሎ በአንድ ጥራዝ ስር የተሰበሰበ ጽሑፍን ሲገልጽ ቅዱስ የሚለው ቃል በእብራይስጥ ክዱስ በሱርስት ካዲሽ በግእዝና በአረብኛ ቅዱስ ከሚለው ቃል የተገኘ ነው። ትርጉሙም የተለየ የተከበረ ማለት ነው።

የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት

ብሉይ ኪዳን ማለት የቆየ፣ የጥንት ውል ወይም ስምምነት ማለት ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን የአንድ አምላክ አማኞች የሆኑትን የዕብራውያንን ታሪክ ያስረዳል። በውስጡም ብዙ የተስፋ ቃሎችን የያዘ ነው። ስለ መሲሕ ክርስቶስ መምጣትም የተነገሩ ትንቢቶች በብዛት አሉበት። ኢሳ 7፡ ፲፬። ብሉይ ኪዳን ከሐዲስ ኪዳን ተነጥሎ አይታይም። ምክንያቱም ብሉይ ኪዳን የሐዲስ ኪዳን ትንቢት ሲሆን ሐዲስ ኪዳን የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ ነው። ሐዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ውስጥ አለ። ሆኖም ግን ነቢያት የተነበዩለት አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘመኑንና ጊዜውን ቆጥሮ በተገለጠ ጊዜ ስውር የነበረው በሐዲስ ኪዳን ተገልጸል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለምን ቅዱስ ተባለ

፩). አስገኝው እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ቅዱስ ተብሏል። ይኸውም የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ቅዱስ ስለሆነ ነው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ። ዘሌ ፩፡ ፺፪። የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። ፩ኛ ጴጥ ፩፡ ፲፭።

፪). ሰውን ወደ ቅድስና የሚያደርስ ስለሆነ ቅዱስ ተብሏል የከበሩ መጽሐፍትን አምኖ መቀበል የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ነው። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው። ራዕ ፩፡ ፳፯።

፫). በእግዚአብሔር መንፈስ የተነሳሱ ቅዱሳን ሰዎች የፃፉት በመሆኑ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ እራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም። ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ። ፪ኛ ጴጥ ፩፡ ፩-፲፩።

፬). የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊት ያለውን ሁኔታ በእርግጠኝነት የሚናገር በመሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ የተከወነ ሁኔታ ሲገለጽ በይሆናል ወይም በግምት ሳይሆን በእርግጠኝነት ነው። እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ እንዳለ። ዘፍ ፩፡ ፩።

፭). ወደፊት ስለሚመጣው በእርግጠኝነት የሚናገር ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያለፈውን በእርግጠኝነት እንደሚያስቀምጥ ሁሉ የሚመጣውንም ድርጊት ያለምንም ጥርጥር በእርግጠኝነት የሚናገር በመሆኑ ልዩ ነው። ሌሎች መጻሕፍት ወደፊት ስለሚመጣው ነገር በእርግጠኝነት ሣይሆን የራሣቸውን መላምት፣ በጥናትና በምርምር ወይም በግምት እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል ቢሉ እንጂ እንዲህ ይደረጋል ብለው በእርግጠኝነት አይናገሩም። ለምሳሌ ነብዩ ኢሣያስ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች (ኢሳ ፯፡ ፲፬) አለ እንጂ ትፀንስ ይሆናል አማኑኤል ሊባል ይችላል አላለም።

፮. የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ስለሚባርክ ሌሎች መጻሕፍትን በማንበብ ምክርና እውቀት ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ እና ቃሉን በመስማት ግን ቡራኬ ይገኛል። ራዕ ፩፡ ፫።

፯.) ዘመን የማይሽረው በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የማያረጅ የዘመን ብዛት የማይገታው ዘላለማዊ ነው። የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ፀንታ ትኖራለች። ኢሳ ፵፡ ፰። ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም። ማቴ ፳፬፡ ፴፭። የጌታ ቃል ለዘለአለም ይኖራል። ፩ኛ ጴጥ ፩፡ ፳፭።

፰) ክብረ ቅዱሳንን የሚዘክር ስለሆነ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ስለቅዱሳን መላእክት፣ ስለቅዱሳን ፃድቃን እና ሠማእታት የሚናገር ነው። በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅድስ የመንፈስ ምግብ ነው። ማቴ ፬፡ ፬፡ ፬፤ ኤር ፲፭፡ ፲፮። የመንገዳችን መብራት ነው። መዝ ፻፲፰፡ ፻፭። በሁለት በኩል የተሣለ ሰይፍ ነው። ዕብ ፬፡ ፲፪። ያንፃል ዮሐ ፲፭፡፫። ያለመልማል። መዝ ፩፡ ፫።

መጽሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈው

የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤቱ እግዚአብሔር ሲሆን ጸሐፊዎቹ ግን ከእርሱ የተላኩ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው። ብዛታቸውም ከዐርባ በላይ ሲሆን አንዳቸውም እንኳን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አልጻፉም። እነርሱም እግዚአብሔር ጻፉ ያላቸውን ጽፈዋል። ለምሳሌ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ጻፍ ተብሎ የጻፈ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ዘጸ ፲፯፡ ፲፬፣ ዘጸ ፴፬፡ ፳፯፣ ዘዳ ፴፩፡ ፲፫። ነቢዩ ኤርምያስም እነሆ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ ብሎ እንደገለጠው እግዚአብሔር የሰጠውን ጽፏል። ኤር ፩፡ ፴። ቅዱስ ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ በማለት የተናገረውም ይህንኑ ያስረዳል። ፪ኛ ጴጥ ፩፡ ፳-፳፩።

መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ቅዱሳን ሰዎች የተለያየ ሥራና አኗኗር እንዲሁም በተለያየ ዘመንና ቦታ የነበሩ ናቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም ጻፉ እየተባሉ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ የነበረባቸው የሥራና የዘመን እንዲሁም የቦታ ልዩነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያንዳቸውም መልዕክት ከሌላው ጋር እንዲጋጭ ባለመደረጉ ዕጹብ ድንቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሥራ ያሳየናል። ከጸሐፊዎቹ መካከል ካህናት፣ ነቢያት፣ ነገስታትና ገበሬዎች ይገኙበታል።

ለምሳሌ ከብሉይ ኪዳን ጸሐፍት ውስጥ ኤርምያስ፣ እዝቅኤልና ዘካርያስ ካህናት ሲሆኑ ሳሙኤል፣ ኢሳያስ፣ ዳንኤልና ሆሴዕ ደግሞ ነቢያት ናቸው። ቅዱስ ዳዊትና ልጁ ሰሎሞን ደግሞ ነገሥታት ናቸው። ከ፲፪ቱ ደቂቀ ነብያት መካከል አንዱ የሆነው አሞጽ ገበሬ/እረኛ/ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጣል። አሞ ፩፡ ፩።

ከሐዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ውስጥም እንዲሁ የተለያየ የሥራ ሙያ የነበራቸው ይገኙበታል። ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ያዕቆብና ፍቅረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ዓሳ አጥማጆች ነበሩ። ሉቃ ፭፡ ፩-፲፩። የሉቃስ ወንጌልንና የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ሐኪም ነበረ። ቆላ ፬፡ ፲፬። ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ደግሞ ቀራጭ /ግብር ሰብሳቢ/ ነበር። ማቴ ፱፡ ፱። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዲስ ኪዳን የመረጣቸው ሐዋርያት ከመጠራታቸው በፊት ያልተማሩ ይሁኑ እንጂ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን በሚገባ ጽፈው አስተምረዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ መቼና የት ተጻፈ

መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ሰዎች እንደተጻፈ ሁሉ የተጻፈበት ዘመንና ቦታም እንዲሁ የተለያየ ነው። የመጀመሪያው መጽሐፍ መጽሐፈ ሄኖክ ከተጻፈበት ከ ፩ሺ፬፲፸፮ ዓ. ዓ. ጀምሮ የመጨረሻው ዮሐንስ ራእይ እስከተጻፈበት እስከ ፺፮ ዓ. ም. ድረስ ብዙ ዘመናት አልፈዋል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ ፬ሺ፩፻ ዓመት በላይ ወስዷል ማለት ነው።

ከላይ እንደተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት እንደተጻፉ ሁሉ የተጻፉባቸው ቦታዎችም እንደዚሁ የተለያዩ ናቸው። ምሳሌ:

ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉባቸው ቦታዎች

  1. የኦሪት መጻሕፍት…………………………………………………………ሲና ምድረበዳ
  2. መጽሐፈ ኢያሱ……………………………………………………………ምድረ ከነዓን (በእስራኤል)
  3. መጽሐፈ አስቴር……………………………………………………………ፋርስ
  4. ትንቢተ ዳንኤል……………………………………………………………ባቢሎን
  5. የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ቆላስይስ………………………………………ሮሜ
  6. ዮሐንስ ……………………………………………………………………ፍጥሞ ደሴት

መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በምን ቋንቋ ተጻፈ

አብዛኞቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በእብራይስጥ ሲሆን ትንቢተ ዳንኤል የተጻፈው ግን በአረማይክ ቋንቋ ነው። የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በዕብራስጥ ከተጻፈው ከማቴዎስ ወንጌልና በሮማይስጥ ከተጻፈው ከማርቆስ ወንጌል ውጭ የተቀሩት የተጻፉት በዘመኑ የአብዛኛው ሕዝብ መነጋገሪያ በነበረው በፅርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነበር።

ከዚህ በላይ ለመግለጽ የተሞከረው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ አመጣጥና መፅሐፍ ቅዱስን ብናጠናና ብናውቅ ከእግዚአብሔር ስለሚያስገኝልን በረከት ነው። ስለምጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትና ብዙ ለማወቅ ወንድ ሲት ወይም ትልቅ ትንሽ ሳይባል ማንኛውም ምዕመን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን በመምጣት ተሳታፊ መሆን የሚችል መሆኑን በደስታ እንገልጻለን።